ኦሮሚያ ባንክና የኢ.ፌ.ድ.ሪ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸዉን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመዋል፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት የኢ.ፌ.ድ.ሪ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚንስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል እና የኦሮሚያ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ክቡር ኦቦ ተፈሪ መኮንን ናቸዉ፡፡
በስምምነት መርሃ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚንስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸዉ ከኦሮሚያ ባንክ ጋር በመተባበር ለውጭ አገር ሥራ ስምሪት ተጠቃሚዎች የፋይናንስ አገልግሎቶችን ማመቻቸት ፤ ከስደት ተመላሽ ዜጎች እና ለቤተሰቦቻቸው የባንክ አገልግሎት መስጠት፣ የክፍያ እና የቁጠባ መፍትሄዎች ማቅረብ እንዲሁም ተደራሽ በሆኑ የገንዘብ የማስተላለፊያ ቻናሎች መደበኛ የገንዘብ ልውውጦችን ማድረግ እና በአጠቃላይ የፋይናንስ ዕውቀት እና የንግድ ልማት አገልግሎቶችን መስጠት የስምምነቱ ማዕቀፍ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ኦሮሚያ ባንክ ደግሞ ዘመኑ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ዉጤቶች መታጠቁ እና ተደራሽ መሆኑ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምርጫ ማድረጉን አክለዋል፡፡
የኦሮሚያ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ክቡር ኦቦ ተፈሪ መኮንንም በበኩላቸዉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ስራ እና አሰሪን ከማገናኘት በተጨማሪ የዜጎቻችን ህይወት መሻሻል ላይ ትርጉም ያለዉ ስራ እየሰራ በመሆኑ ያላቸዉን አድናቆት ገልፀዋል፡፡ ኦሮሚያ ባንክም ማህበረሰብ አቀፍ ባንክ በመሆኑ ስምምነቱ ዉስጥ ከተጠቀሱት አንኳር ጎዳዮች ባሻገር የዜጎቻችን ህይወት የሚያቃኑ ስራዎች መስራት ባንኩ የተቋቋመለት አላማ በመሆኑ በልዩ ትኩረት እንሰራለን ብለዋል፡፡
አክለዉም የኦሮሚያ ባንክ እና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በጋራ ከሚሰሩባቸዉ ጉዳዮች መካከል ፤ በሥራ ቅጥር ዙሪያ፣ በክህሎት ማጎልበት እና ፋይናንሺያል ተደራሽነት ለጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች፣ ለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተመራቂዎች እና ለሥራ ፈጠራ ባለቤቶች ጭምር ትብብርን ያጠቃላል ብለዋል።

