1. News and Updates
  2. የኢትዮጵያ እሰልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር ዶ/ር ሼክ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ የፊኒሺንግ ስራዉ እየተጠናቀቀ የሚገኘዉን የኦሮሚያ ባንክ የሽግግር ዋና መስሪያ ቤት ጎበኙ፡፡
ከባንኩ መስራቾች አንዱ የሆኑት እና ለረጅም ጊዜ የኦሮሚያ ባንክ የሸሪያ አማካሪዎች ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን እያገለገሉ ያሉት ክቡር ዶ/ር ሼክ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፥ በመሃል ፊንፊኔ ጎማ ቁጠባ አከባቢ እየተገነባ የሚገኘዉን ባለ 35 ወለሉ የባንኩ የሽግግር ዋና መስሪያ ቤት ጐብኝተዋል፡፡
ከጉብኝቱ በኃላ ክቡር ዶ/ር ሼክ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኦሮሚያ ባንክ የሙስሊሙ ማህበረሰብ የዘመናት ጥያቄ የሆነዉን ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በሀገራችን በመጀመር ፈር ቀዳጅ ባንክ መሆኑን አንስተዉ፤ ዛሬ የተሟላ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለሚሰጡ ባንኮች መሰረት የጣለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት 17 ዓመታት ኦሮሚያ ባንክ ያሳለፉቸው የእድገት እና የስኬት ጉዞዎች እጅግ አስደናቂ ናቸዉ ያሉት ክቡር ዶ/ር ሼክ ሀጂ፤ ባንኩ ባለ 35 ወለል ግዙፍ ህንፃ በመሀል ፊንፊኔ ማስገንባቱ ለእድገቱ እና ስኬቱ ዋንኛ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የኦሮሚያ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አሰፋ ስሜ በበኩላቸዉ፥ የሽግግር ዋና መስሪያ ቤቱ ወሳኝ የግንባታ ምዕራፍ የሆነዉ የፊኒሺንግ ስራዉ እየተቀላጠፈ እንደሚገኝ ጠቅሰዉ ግንባታዉ በተቀመጠለት የግዜ ሰሌዳ እና የግንባታ ጥራት እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ም/ሰብሳቢ እና የኖሚኔሽን እና ሪሙኒሬሽን ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኦቦ እሸቱ ዘለቀ በበኩላቸዉ ህንፃ ህንፃዉ ዘመኑ የደረሰበት የግንባታ ቴክኖሎጂ በመጠቀም እየተገነባ እንደሚገኝ ገልጸዉ በፍጥነት ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ እንዲሆን ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኦቦ ተፈሪ መኮንን በበኩላቸዉ ባንኩ ካስመዘገባቸው ጉልህ ስኬቶች መካከል እንደ አንዱ የሚቆጠረዉ የሽግግር ዋና መስሪያ ቤት ግንባታ፤ በከፍተኛ ጥራት እና ፍጥነት እየተገባደደ እንሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ወሳኝ የዉስጥ ሰራዎችን በማጠናቀቅ መስታወት የማልበስ ስራ በጥራት እየተገባደደ እንደሚገኝ የጠቀሱት ኦቦ ተፊረ፥ ክቡር ሼክ ሀጂ በዚህ በረመዷን የፆም ወክት ደከመኝ ሳይሉ ሁሉንም የግንባታዉን ክፍሎች ስለጎበኙ አመስግነዋል፡፡
በ2,200 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈዉ ባለ 35 ወለሉ የኦሮሚያ ባንክ የሽግግር ዋና መስሪያ ቤት፤ ከባንኩ ሜጋ ፐሮጀክቶች መካከል አንዱ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ዉስጥ የማጠቃለያ ስራዉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ይሆናል ተብሏል፡፡
ህንፃዉ በያዘዉ ገዢ እና ከፍታ ቦታ መዲናችንን ሙሉ በሙሉ በማሳየት፤ ለከተማችን አዲስ የእይታ አድማስ እና ዉበት እንዲሁም ለሀገራችን ተጨማሪ ኩራት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

Pin It on Pinterest

Share This

Share This

Share this post with your friends!

Share This

Share this post with your friends!

×