በዓመታዊ ግምገማዉ ላይ የቀጠና ጽ/ቤት እና ቅርንጫፎች የስራ አፈፃፀም ሪፓርት ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል። ባንኩ የ2024/25 የበጀት ዓመት 3.3 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማስመዝገቡን በጉባዔው ላይ ተገልጿል። ይህም በባንኩ ታሪክ ከፍተኛ ዉጤት ሆኖ ተመዝግቧል።
የኦሮሚያ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኦቦ ተፈሪ መኰንን፤ ባንካችን ያለፈውን የበጀት ዓመት ሀገራዊ እና አለም አቀፋዊ ፈተናዎችን ተቋቁሞ አስደናቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል። በዲጅታል ተደራሽነት፣ በብድር አመላለስ፣ በጤናማ ብድር ምጣኔ፣ በፕሮጀክት አፈጻጸም፣ በህግ አክባሪነት የተሻለ ዉጤት መመዝገቡንም ገልፀዋል።
ኦቦ ተፈሪ አክለውም ለተገኘዉ ውጤት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት፤ ደንበኞቻችን፣ የስራ ዓመራር ቦርድ አባላት ፣ ማኔጅመንት እና መላዉ የባንኩን ሰራተኞችንም አመስግነዋል፡፡
የኦሮሚያ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ም/ሰብሳቢ አቶ እሸቱ ዘለቀ በበኩላቸው በአዲሱ የበጀት ዓመት የባንኩን የአገልግሎት አሰጣጥ ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ለደንበኞች ምቹ እና ቀልጣፋ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ትኩረቱን የሀብት አስባሰብ ላይ በማድረግ እንዲሰራ አሳስበዋል።
በባንኩ ሰራተኞች መካከል የውድድር መንፈስ ለማስረፅ በዋና ስራ አስፈፃሚያችን ኦቦ ተፈሪ መኮንን ሀሳብ አመንጪነት ሲካሄድ የቆየው የCEO CHALLENGE የፕሬዝዳንሺያል አዋርድ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የቀጠና ፅ/ቤት፣ ቅርንጫፎች እና ዋና መ/ቤት ሰራተኞች ማበረታቻ እና ዕውቅና በመስጠት ጉባኤው ተጠናቋል።

