1. News and Updates
  2. የኦሮሚያ ባንክ የትርፍ ምጣኔ ከባለፈው የበጀት አመት ጋር ሲነፃፅር የ49 በመቶ እደገት እንዳለው ተመላከተ፡፡

ባንኩ በ2025/2026 የበጀት ዓመት በሁሉም ዋና ዋና ቁልፍ የአፈፃፀም መለከያዎች አመርቂ ዉጤት ማስመዝገቡን አስታወቋል፡፡

ባንኩ 17ኛዉን መደበኛ እና 6ኛ አስቸኳይ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔዎች በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል አካሂዷል፡፡
የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አስፋ ስሜ ለጠቅላላ ጉባዔው የዳይሬከትሮች ቦርድ አመታዊ የስራ ሪፓርት አቅርበዋል።
የፋይናንስ ዘርፉ በአለም አቀፍ እና ሀገራዊ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ቢገኝም ኦሮሚያ ባንክ ለፈተናዎቹ ሳይበገር ባስቀመጣቸዉ ቁልፍ የአፈፃፀም መለኪያዎች የላቀ ዉጤ አስመዝግቧል፡፡ በተለይም የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴ እጥረት የሀገራችንን ባንኮች በከፍተኛ ሁኔታ ቢፈታተንም፤ ኦሮሚያ ባንክ ፈተናዎቹን ተቋቁሞ ጥራት ያለዉ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የባንክ አገልግሎት በመስጠት የላቀ የአገልግሎት ማዕከልነቱን አስጠብቆ ቀጥሏል፡፡
በዋና ዋና ቁልፍ መለኪያዎች ስንመለከት የባንኩ ጠቅላላ ሀብት ከ105.7 ቢሊዮን ብር በላይ የተሸገረ ሲሆን ባለፈዉ ዓመት የበጀት ዓመት ከነበረዉ የ24 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡ አጠቃላይ የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ብር 70.3 ቢሊዮን በ24% በማደግ 88.1 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

የባንኩ የተከፈለ ካፒታል በ14% በማደግ 7.8 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ አጠቃላይ ካፒታል ደግሞ 14 ቢሊዮን ብር ማድረስ ተችሏል፡፡
በሂሳብ ዓመቱ 15.24 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ገቢ የተገኘ ሲሆን፣ ይህም የዕቅዱን 99.9% ማሳካት ተችሏል፡፡ ይህም ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ23.3 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ ጠቅላላ ወጪው 11.42 ቢሊዮን ብር ነበር። ይህ አፈፃጸም በዲሲፕሊን እና በጥበብ ከተመራው የወጪ አስተዳደር ጋር ተዳምሮ፣ ከታክስ በፊት 3.82 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ትርፍ አስገኝቷል፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ49 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡

ባንኩ የገቢ እና ወጪ መዋቅሩን በማስተካከል የገቢ እና ከታክስ በፊት የተገኘው የትርፍ ዕድገት ከወጪ ዕድገት በእጅጉ እንዲበልጥ በማስቻል ጠንካራ የፋይናንስ መሠረት እንዲገነባ እና የረጅም ጊዜ እሴት ለመፍጠር ጠንካራ መሠረት ጥሏል።

የአዳዲስ ደንበኞቻችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ያደገ ሲሆን፣ የተቀማጭ ሂሳቦቻችንን (deposit accounts) በ9.72% በማደግ 7.54 ሚሊዮን ድርሷል። የባንካችን የዲጂታላይዜሽን አፈፃጸም በእጅጉ እየተፋጠነ ሲሆን፣ የዲጂታል አገልግሎቶች ተጠቃሚ ደንበኞቻችን ቁጥር 5.7 ሚሊዮን ደርሷል።

የባንካችን ልዩ መለያ እና መወዳደሪያ እየሆነ የመጣዉ ተቋማዊ ጤንነታችን ዘንድሮም እንደወትሮዉ በተሻለ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡ የባንካችን የተበላሸ ብድር (NPLs) 2.43% የነበረ ሲሆን፣ ይህም በኢትዮጵ የባንክ ኢንዱስትሪ የተሻለ የብድር ጥራት ካላቸው ቀዳሚ ባንኮች ተርታ ያሰልፈናል።

ከፊንቴክ አጋሮቻችን ጋር በመተባበር  አባ ፈርዳ ሬሚት የተሰኘ የሬሚታንስ አገልግሎት የሚያቀላጥፍ  መተግበሪያ ስራ ላይ ዉሏል፡፡ ባንካችን ኦሮሚያ ባንክ፤ በአለም አቀፍ የዲጂታል ክፍያ ዘርፍ መሪ ከሆነው ቪዛ (Visa) እና በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በቪዛ እውቅና ያገኘ የሶስተኛ ወገን የክፍያ አሳላጭ (third-party processor) ከሆነው ፕሪሚየር ስዊች ሶሉሽንስ (PSS) ጋር በመተባበር ለአለም አቀፍ የካርድ ተጠቃሚ ደንበኞች የሚዉል ኦሮ ቪዛ ክላሲክ፤ ኦሮ ቪዛ ጎልድ እና ኦሮ ቪዛ ፕላቲንየም የተሰኙ ዓለም አቀፍ የክፍያ ኮርዶችን ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡

ጎማ ቁጠባ አከባቢ የሚገኘው ባለ 35 ወለል የሽግግር ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ መዋቅራዊ ግንባታው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ የማጠናቀቂያ ስራዎች (finishing works) በተፋጠነ ሁኔታ በመካሄድ ላይ መሆኑን እና በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የህንጻው ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም፣ ገላን ከተማ በሚገኘው 19 ሄክታር የባንኩ ይዞታ ላይ የሚገነባው  የልህቀት እና ኮንቬንሽን ማዕከል የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ፣ ማለትም የግምጃ ቤት፤ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ እና የጋራዥ አገልግሎት ግንባታዎች ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቀው ስራ ላይ ይገኛል። የሁለተኛው ምዕራፍ የባለ ዘጠኝ ወለል (B+G+9) ቅይጥ (mixed use) አገልግሎት  ሕንጻ ተመርቆ ለአገልገሎት ዝግጁ ሆኗል፡፡

ባንካችን እንደተለመደው ተቋማዊ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገውን ጥረትም አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ በሪፖርት ዓመቱ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ወጪ በማድረግ በተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ በማድረግ ህዝባዊነቱን አረጋግጠዋል፡፡

ዛሬ በተካሄደው የባንኩ ጠቅላላ ጉባዔ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው የኮርፓሬት ገቨርነንስ  መመሪያ ቁጥር  SBB/91/2024 መሠረት ለቀጣይ 3 ዓመታት ባንኩን የሚመሩ የዳይሬክትሮች ቦርድ አባላት ምርጫ በማካሄድ ጉባዔው ተጠናቋል።

Pin It on Pinterest

Share This

Share This

Share this post with your friends!

Share This

Share this post with your friends!

×