የኦሮሚያ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት በባንካችን እየተገነቡ የሚገኙ ሜጋ ፕሮጀክቶችን እና የኢንፎረሜሽን ሲስተም መሰረተ ልማቶችን ጎበኙ
ከተጎበኙት ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል በመሃል ፊንፊኔ ጎማ ቁጠባ አከባቢ የፊኒሺንግ ስራው እየተቀላጠፈ የሚገኘው፤ ባለ 35 ወለል የኦሮሚያ ባንክ የሽግግር ዋና መስሪያ ቤት ህንፃ ይገኝበታል፡፡ ይህ የባንኩ የሽግግር ዋና መስሪያ ቤት ግዙፍ ህንፃ፤ በ2200 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን ከአጠቃላይ ሥራው 32 በመቶ የሚይዘው የኮንክሪት ሙሌት ስራዉ ከጥቂት ወራት በፊት ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ፤ የፊኒሽንግ ስራዉ 20 በመቶ ላይ የደረሰ ሲሆን አጠቃላይ ፕሮጀክቱ 52% ላይ ደርሷል። ህንፃዉ በያዘዉ ገዢ ቦታም ለባንካችን ተጨማሪ አዲስ ከፍታ፣ ለከተማችን አዲስ የእይታ አድማስ እና ዉበት፣ ለሀገራችን ተጨማሪ ኩራት ነው ተብሏል።
በባንካች የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ከተጎበኙት ፕሮጀክቶች መካከል በኦሮሚያ ባንክ እየተገነባ የሚገኘዉ በ20 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈዉ የገላን የልህቀትና ኮንቬንሽን ማዕከል (Gelan Excellence and Convention Centre) ይገኝበታል።
የማዕከሉ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ተጠናቆ የሁለተኛዉ ምዕራፍ ባለ B+G+9 ወለል ግዙፍ ሁለገብ ህንፃ በከፍተኛ ፍጥነት እየተገነባ ነው። ህንፃውን ለመጨረስ የተያዘለት ጊዜ 22.5% የደረሰ ሲሆን ህንፃው ግን ከተያዘለት ጊዜ በመፍጠን በአሁን ጊዜ 40 በመቶ ላይ ደርሷል።
በተጨማሪም በሰንጋ ተራ ፋይናንሺያል ዲስትሪክት አከባቢ ለባንካችን ዋናዉ መስሪያ ቤት ህንፃ መስሪያ ቦታ የሚሆን በቅርቡ ባንካችን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተረከበዉ ሰፊ ቦታ በቦርድ አባላት ከተጎበኙ ቦታዎች መካከል ይገኝበታል።
ባንካችን ደህንነቱ የተጠበቀ ጠንካራ 24/7 አገልግሎት የሚሰጥ የመረጃ ቋት ( Tier 3 data center) መሰረተ ልማት ቀድመዉ ከገነቡ ጥቂት የፋይናንስ ተቋማት መካከል ይገኛል፡፡ በዚህም ዘመኑን የዋጀ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የደረጀ ዳታ ሴንተር መሰረተ ልማት ከነ ዳታ ሪከቨሪ በመታጠቅ የባንኩን የመረጃ አያያዝ ከማዘመኑም ባሻገር 99.982% የማይቃረጥ አገልግሎት የሚስጥ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ባንኩ የታጠቀው ዳታ ሴኪውሪቲ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ያሟላ በመሆኑ ጥቃቶችን 24/7 በመከታተል፣ በመለየትና በማምከን የሚከላከል በመሆኑ የባንኩን የመረጃ አያያዝና ጥበቃ አስተማማኝ እንዲሆን አስችሎታል።ይህ ዘመናዊ የዳታ ሴንተር መሰረተ ልማትም በባንካችን የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ተጎብኝቷል።
ባንካችን የዘመናዊ ዳታ ሴንተር ባለቤት መሆኑ የደንበኞቹን እምነት ከፍ የሚያደርግ ሲሆን፣ የፊኒሺንግ ሥራው እየተቀላጠፈ የሚገኘው የኦሮሚያ ባንክ የሽግግር ዋና መሥሪያ ቤት ሰማይ ጠቀስ ህንፃ እና በገላን ከተማ 20 ሄክታር መሬት ላይ እየተገነባ የሚገኘው በዓይነቱ ለየት ያለው ሁሉን አቀፍ አገልግሎት የያዘው ግዙፉ የልህቀት እና የኮንቬንሽን ማዕከል ፕሮጀክት የባንኩን ሀብት ከመጨመራቸው በተጨማሪ ለሀገራችን የግንባታ እና መሰረተ ልማት እድገት የጎላ ሚና ይኖራቸዋል።

